የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት

በዴንቨርና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ሥርዓተ አምልኮታቸውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናና ዶግማ መሠረት ለመፈጸም ጥረት ያላደረጉበት ወቅት የለም። ይሁን እንጂ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋረጡ በተለያዩ ጊዜያቶች ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈዋል።

በፖለቲካና በዘር በመከፋፈልና በመበጣበጥ የሰላም የፍቅርና የአንድነት ማዕከል የሆነችው የእግዚአብሔር ቤት የጥቂት ግለሰቦች ቤትና ንብረት እስከመሆን ደረጃ ደርሳ ነበር። የዚህ ዓይነቱ በፖለቲካና በዘር የመከፋፈል መጥፎ በሽታ ከቤተ ክርሰቲያን ሥርዓት መጣስ ጋር እየተስፋፋ መምጣቱ አግባብ አለመሆኑን በሚቃወሙና ለሃይማኖታቸው ቀናዕያን በሆኑ ምእመናን ላይ በወቅቱ ብዙ ፈተናና በደል ደርሶባቸው ነበር። ከዚህ ችግር የተነሣ በብስጭት ከችግሩ የሸሹ መስሎአቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጠልተው በየቤታቸው የቀሩ ምእመናን ቁጥር እየበዛ በመምጣቱ ፤ በሌላ በኩል ከእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በፖሊስ ኃይል በግዴታ እንዲባሩ መደረጉ ችግሩን የከፋ አደረገው።

በመሆኑም በወቅቱ ይህንን ችግር የተመለከተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በሰሜን አሜሪካ በዴንቨር ቀጣና ማዕከል አማካይነት መምህራንን እየጋበዘ ትምህርታዊ ጉባኤያትን በማዘጋጀት ምእመናን መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ባሉበት እንዲጸኑ ከፍተኛ እገዛን ሲያደርግ ቆየ።

ችግሮች ተወግደው ሰላም ሰፍኖ ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ከዛሬ ነገ እንመለሳለን በማለት ለተወሰኑ ዓመታት ምእመናን ቢታገሱም ችግሮቹ እየተባባሱ ከመምጣት በስተቀር የተሻለ ነገር ባለመታየቱ ፤ በተለይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የምትሰጣቸውን መንፈሳዊ አገልግሎቶች እንደ ክርስትና ፣ ጋብቻና ፍትሐት የመሳሰሉትን ብዙዎች ምእመናን በመነፈጋቸው ችግሩን ይበልጥ አስከፊ አደረገው።

ከዚህም የተነሣ በሰላም በፍቅርና በአንድነት እግዚአብሔርን የምናመልክበት የራሳችን የሆነ ቤተ ክርስቲያን ለምን አይኖረንም ? የሚል ጥያቄ ከአብዛኛው ምእመን ቀረበ። ይህም ጥያቄ በወቅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለነበሩት ለብፁዕ አቡነ ማትያስ ቀረበ። ብፁዕነታቸውም በዴንቨር ኮሎራዶ የነበረውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት በቂ ጊዜ ወስደው ጉዳዩን ካጠኑ በኋላ ጥያቄውን በደስታ ተቀበሉት። በመጨረሻም ሚያዚያ ፪ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. ( April 10 2005 ) ኮርያኖች ይገለገሉበት የነበረውን ቸርች በመከራየት ብፁዕነታቸው ባርከውና ቀድሰው ስሙንም በዴንቨር ኮሎራዶ ደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ እንዲጠራ ሰይመው ተከሉ።

ከቤተ ክርስቲያኑ ምሥረታ ማግስት በኋላ ደግሞ ሌላ ትልቅ ችግር ዓይኑን አፍጦ መጣ። በመጀመሪያ ለአገልግሎት የተከራየነውን የኮርያኖችን ቸርች ከእንግዲህ በኋላ ለአገልግሎት መጠቀም እንደማንችል ተነገረን። በሌላ በኩል ደግሞ ቀድሰው የሚያቆርቡና የሚያስተምሩ ካህናት አባቶችን ፈለጎ ማግኘት ተራራን የመግፋት ያህል ከባድ ሆኖ ያስጨንቀን ጀመር። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት ቸርች ኦፍ ዘ ኮቨነንት በሚል ስያሜ በሚጠራ አንድ ሕንጻ ውስጥ ትንሽዬ ክፍል ተከራይተን ገባን። ካህናት አባቶችም ከሌላ እስቴት በየሳምንቱ እየሙጡ ለ፮ ወራት ለአንድ ሳምንት እንኳን ቅዳሴው ሳይተጓጐል አገልግሎቱ ቀጠለ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለመንጋዎቹ ግድ የሚለው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ባላሰብነውና ባልጠበቅነው ሁኔታ መንጋዎቹን በቅርብ ሆነው የሚከታተሉ ከበረታቸው እንዳይወጡ የሚጠብቁ ካህናት አባቶችን ሰጠን። ትልቁን ችግር በድል መራመድ ስንጀምር የተከራየነው ሕንጻ ኪራዩ በመጨመሩ ሌላ ሕንጻ መፈለግ ግድ ሆነ። ይህም ባሰብነው ፍጥነት ተሳክቶ ሌላ ሕንጻ ተከራይተን መገልገል ጀመርን።

ታኅሣሥ ፱ ቀን ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ከጊዜያዊ ሰበካ ጉባኤኃላፊነቱን የወሰደው አዲሱ ሰበካ ጉባኤ ሥራውን ሲረከብ ቤተ ክርስቲያኑ የፋይናንስ ችግር ላይ የነበረበትና በተጨማሪም የነበርንበት የኪራይ ቤት ከአብዛኛው ምእመን መኖሪያ አካባቢ የራቀ ስለነበረ ሌላ ሕንጻ ማፈላለግ ጀመረ።

በወቅቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከራይ ሕንጻ አፈላልጐ ማግኘቱ እጅግ ከባድ ስለነበር ከዚህ ቀደም በኪራይ ዋጋ ውድነት ምክንያት ተለቆ የነበረውን የቸርች ኦፍ ዘኮቨነንት ሕንጻ ባለቤቶችን የኪራዩን ዋጋ ቅናሽ እንዲያደርጉ ያቀረብንላቸውን ሐሳብ በመቀበላቸው የአንድ ዓመት ኮንትራት በመፈራረም በአንጻሩም እኛ አቅማችንን በማሰደግ የራሳችን የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መግዛት እንዳለብን በማመን ሰበካ ጉባኤው አቋም ወሰደ።

በዚህም መሠረት የነበረውን የፋይናንስ ችግር በተቻለ መጠን በአስቸኳይ ለመቅረፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎቸን በማድረግ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ250,000 ሺህ ዶላር በላይ ለሕንጻ መግዣ የሚውል ገንዘብ ማሰባሰብ ተቻለ።

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ፣ እምነትና ትውፊት መሠረት እንደ ልባችን ሆነን አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም የሚያስችለንን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመግዛት የሕንጻ ግዢ ኮሜቴ በማዋቀር ከሰበካው ጉባኤ ጋር በመሆን አብሮ መሥራት ጀመረ። ይህ ከምንም በላይ የሆነው ታላቅ ጅማሬ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ሥራው በተጀመረ በዓመቱ በእግዚአብሔር ቸርነት 950,000 ሺህ ዶላር ለመግዛት ተደራድረን የነበርነውን ሕንፃ በ800,000 ሺህ ዶላር በመግዛት እልባት አግኝቶ ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፪፼ ዓም (January 6, 2008) በወቅቱ በሰሜን አሜሪካ የምዕራብና ካሊፎሪኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተባርኮ ታቦተ ሕጉ ገባ።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ? እንዳለ ለእኛ የተደረገልን እጅግ ምጡቅና ከአእምሮ በላይ በመሆኑ ሁሌም አምላካችንን እናመሰግነዋለን። ዕውቀቱም ሆነ ገንዘቡ ሳይኖረን ከትቢያ ላይ አንስቶ ከፍ ከፍ አድርጐናልና ክብርና ምሥጋና ይድረሰው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር